Announcement የ2019 ዓ.ም የ90 ቀናት ዕቅድ

የ2019 ዓ.ም የ90 ቀናት ዕቅድ

12th July, 2026

የደጃዝማች ገረሱ ዱኪ ኢንዳስትሪያል ኮሌጅ የ2019 ዓ.ም የ90 ቀናት ዕቅድ ላይ ከአመራሮች ጋር ተወያየ
በአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር በስራና ክህሎት ቢሮ ስር የሚገኘው የደጃዝማች ገረሱ ዱኪ ኢንዳስትሪያል ኮሌጅ፣ የ2019 ዓ.ም የ90 ቀናት (ከሐምሌ 1/2018 እስከ መስከረም 30/2019 ዓ.ም) የንቅናቄ ዕቅድ ላይ ከአካዳሚክ ኮሚሽን እና ማኔጅመንት አባላት ጋር የጋራ ውይይት አድርጎ አጸደቀ።
ይህ የ3 ወራት የንቅናቄ ዕቅድ የስልጠና ጥራትና አግባብነትን ለማረጋገጥ እንዲሁም ፍትሃዊነትና ተደራሽነትን ለማሳደግ ታስቦ የተዘጋጀ መሆኑ ተገልጿል። ከመደበኛ ዕቅድ ጎን ለጎን ትኩረት ተሰጥቷቸው መከናወን ያለባቸውን ተግባራት በቅንጅት ለመፈጸም የሚያስችል መሆኑም ተጠቁሟል።
በውይይቱ የጸደቀው ዕቅድ ዋና ዋና ግቦች የሚከተሉትን ያካትታሉ፡-
በ2018 የስልጠና ዘመን ስልጠናቸውን ያጠናቀቁ 255 ሰልጣኞችን የሞዴል ምዘና በማስወሰድ ማብቃት፣ እንዲሁም የሙያ ብቃት ማረጋገጫ ምዘና እንዲወስዱ በማድረግ ብቃታቸውን አረጋግጦ በአንድ ማዕከል ማስመረቅ።
የክህሎት ስልጠና ለሚያስፈልጋቸው 5,000 ሥራ ፈላጊዎች የልል ክህሎት ስልጠና መስጠት።
ከእነዚህ 5,000 ስራ ፈላጊዎች ውስጥ 1,000 የሚሆኑት የቴክኒክ ክህሎትና የኢንተርፕረነርሺፕ ስልጠና እንዲያገኙ ማድረግ።
የስልጠና ጥራትን ለማረጋገጥ የአሰልጣኞችን የክህሎት ክፍተት በመለየትና የፕሮጀክት ቤዝድ ስልጠና በመስጠት አቅማቸውን መገንባት።
የኮሌጁን 26 አመራሮች (የስልጠና ዘርፍ ተጠሪዎች፣ አስተባባሪዎች፣ ዲሬክቶሬቶችና የቡድን መሪዎች) አቅም ማጎልበት።
መቅጠር ከሚችሉ ኢንዱስትሪዎች ጋር የተጠናከረ ትስስር እና አውደ ርዕይ በማዘጋጀት 50% የሚሆኑ ተመራቂ ሰልጣኞችን ከስራ ጋር ማስተሳሰር።
ለ2019 የስልጠና ዘመን 900 አዳዲስ ሰልጣኞችን ለመቀበል በ3ቱም ክፍለ ከተሞች የንቅናቄ መድረኮችን በማዘጋጀትና ከተመረጡ 8 ሁለተኛ ደረጃ ትምህርት ቤቶች ጋር በቅንጅት በመስራት ግንዛቤ መፍጠር።
በኮሌጁ ውስጥ የሚጠገኑ ማሽነሪዎችን በመለየትና አስፈላጊውን ግብዓት በማፈላለግ የጥገና ስራዎችን በውስጥና በውጭ አቅም ማከናወን።
ኮሌጁ የተሰጠውን ብቁ የሰው ኃይል የማፍራት ተልዕኮ በብቃት ለመፈጸም፣ የማሰልጠኛ ወርክሾፖችን በስታንዳርድ በማደራጀትና የአሰልጣኙን ሙያዊ አቅም በመገንባት ላይ ትኩረት አድርጎ እንደሚሰራ በዕቅዱ ማብራሪያ ላይ ተመላክቷል። የድርጊት መርሐ-ግብሩም ተግባራቱ ከሐምሌ 1ኛ ሳምንት ጀምሮ እስከ መስከረም 4ኛ ሳምንት ድረስ በምን አግባብ እንደሚፈጸሙ በግልጽ አስቀምጧል።

 

.

Copyright © All rights reserved.

Created with