Announcement "ተስፋን እንትከል"

"ተስፋን እንትከል"

11th July, 2026

"ተስፋን እንትከል" - የደጃዝማች ገረሱ ዱኪ ኢንደስትሪያል ኮሌጅ ማኅበረሰብ በአረንጓዴ አሻራ መርሐ ግብር አሻራውን አሳረፈ
አዲስ አበባ፤ ሰኔ 29 ቀን 2018 ዓ.ም.
ኢትዮጵያ በየዓመቱ በከፍተኛ ንቅናቄ እያካሄደችው የምትገኘው የአረንጓዴ አሻራ መርሐ ግብር ዘንድሮ ለ8ኛ ዙር በተሳካ ሁኔታ እየተከናወነ ይገኛል። ይህንን ታላቅ ብሔራዊ ጥሪ ተከትሎ፣ "ተስፋን እንትከል" በሚል መሪ ቃል በመላ ሀገሪቱ እየተደረገ ባለው የችግኝ ተከላ ንቅናቄ ላይ የደጃዝማች ገረሱ ዱኪ ኢንደስትሪያል ኮሌጅ ሙሉ ማኅበረሰብ በንቃት በመሳተፍ አረንጓዴ አሻራውን አሳርፏል።
የኮሌጁ አመራሮች፣ መምህራንና ሠራተኞች በኮሌጁ ቅጥር ግቢ ውስጥ የተለያዩ የፍራፍሬ ችግኞችን በመትከል፣ የአካባቢ ጥበቃንና የልማት ተምሳሌትነታቸውን በተግባር አሳይተዋል።
"
ይህ መርሐ ግብር የአየር ንብረት ለውጥን ለመቋቋም ወሳኝ ነው" — አቶ መስፍን ቸሩ (ዋና ዲን)
በችግኝ ተከላው መርሃ ግብር ላይ ተገኝተው መልዕክት ያስተላለፉት የደጃዝማች ገረሱ ዱኪ ኢንደስትሪያል ኮሌጅ ዋና ዲን አቶ መስፍን ቸሩ እንደገለጹት፤ የአረንጓዴ አሻራ መርሐ ግብር መሬትን ከምርታማነት ባለፈ የዓለም ስጋት የሆነውን የአየር ንብረት ለውጥን ለመቋቋም ያለውን ፋይዳ ገልጸዋል። የኮሌጁ ማኅበረሰብም ይህንን ታሪካዊና ሀገራዊ ጥሪ እንደ አንድ ትልቅ የማኅበራዊ ኃላፊነት በመውሰድ፣ ለቀጣይነቱና ለስኬታማነቱ በቁርጠኝነት እንደሚሠራ አረጋግጠዋል።
"
የምንተክላቸው ችግኞች እንዲጸድቁ የኮሌጁ ክትትልና እንክብካቤ አይለይም" — አቶ ታከለ ኦላኒ (የተቋማት ልማት ምክትል ዲን)
የኮሌጁ የተቋማት ልማት ምክትል ዲን አቶ ታከለ ኦላኒ በበኩላቸው፤ የችግኝ ተከላው የአካባቢን የተፈጥሮ ሚዛንና ውበት ከመጠበቅ ባለፈ ለቀጣዩ ትውልድ የሚተላለፍ ትልቅ "የተስፋ ስንቅ" መሆኑን ገልጸዋል። አክለውም፦
"
የእኛ ተሳትፎ ችግኝ በመትከል ብቻ የሚያበቃ አይደለም፤ የተከለናቸው ችግኞች በሙሉ ጸድቀው ለታለመላቸው አረንጓዴ ልማት እንዲበቁ የኮሌጃችን ማኅበረሰብ ቀጣይነት ያለው የኮትኮታና የእንክብካቤ ሥራዎችን በባለቤትነት ያከናውናል" ሲሉ አስገንዝበዋል።
የደጃዝማች ገረሱ ዱኪ ኢንደስትሪያል ኮሌጅ በቴክኖሎጂና በኢንዱስትሪ ሥልጠና ከሚሰጠው ሰፊ አስተዋጽኦ ጎን ለጎን፣ እንደዚህ ባሉ ሀገራዊና አካባቢያዊ የልማት ሥራዎች ላይ ግንባር ቀደም ተሳታፊነቱን አጠናክሮ እንደሚቀጥልም በዕለቱ ተገልጿል።

.

Copyright © All rights reserved.

Created with